የባህርዳር ከነማ እና የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋች የሆነው አለልኝ አዘነ በትውልድ ከተማው አርባምንጭ አርፏል።
አለልኝ ጥሩ የሆነ ኘሮፌሽናል ብሎም ደግሞ ባለው አቅም ለትልቅ ደረጃ የሚጠበቅ ተጫዋች እንደነበር በቅርብ የሚያቁት ይናገራሉ፤ ባሳለፍነው አመት ባህርዳር ከነማ በሊጉ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ ነበር፤ ይሄ ሚናውም የአመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ሲመረጡ የመጨረሻዎቹ 5 ምርጥ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ስሙ እንዲካተት አስችሎታል።
አለልኝ ህይወቱ በድንገት እስካለፈባት ጊዜ ድረስ የ' Anterior cruciate ligament(ACL) ' ጉዳት ካጋጠመው በኋላ ወደትውልድ ከተማው አርባምንጭ ሄዶ ቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ህክምናውን እየተከታተለ ይገኝ ነበር። ትክክለኛ የአሟሞቱን ሁኔታ በተመለከተ የህግ ሰዎች ጉዳዩን ይዘውታል።
አለልኝ ለአርባምንጭ ከነማ የተለያዩ የእድሜ እርከን ቡድኖች ውስጥ ፈጣን እድገት በማሳየት መጫወት የቻለ ሲሆን ከአርባምንጭ በመቀጠል የሁለት ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ወደሆኑት ወደ ሀዋሳ ከነማ ነው ያመራው፤ ከ3 አመት በፊት ደግሞ የጣና ሞገዶቹን ተቀላቅሎ ጥሩ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ ችሏል።
አለልኝ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሲሆን ኢትዮጵያን ወክሎ ሞሮኮ በተካሄደው በቻን አፍሪካ ዋንጫ ላይ መሰለፍ ችሏል፤ እንደ ቡድን ጓደኞቹ ገለፃ ከሆነ አለልኝ ትልቅ ታለንት ያለው፤ ኘሮፌሽናል እና ትሁት መሪ ነው። የዘንድሮው ውድድር ዘመን ሲጀምርም በክለቡ የምክትል አምበልነት ማእረግን ማግኘት ችሏል።
አለልኝ ከወር በፊት ነበር አዲስ አበባ በሚገኘው ቦሌ መዶሀኔአለም ከረጅም ጊዜ ፍቅረኛው ጋር በቤተ- ክርስትያን ስርአት የተጋባው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የሊጉ አክሲዮን ማህበር፣ የተለያዩ ክለቦች እና ሌሎች የእግር ኳሱ ቤተሰቦች በአለልኝ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።
ባለፈው ሳምንት ከተደረጉ ሁሉም የሊጉ ጨዋታዎች በፊትም የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
Via AIPS Media
© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu