ቴክኒካዊ ትንታኔ
ማይኖ የቀኝ እግር አማካይ ሲሆን ለእንግሊዙ ክለብ ማንቺስተር ዩናይትድ ዋናው ቡድን በተከላካይ አማካይነት በብዛት ሲጫወት ይስተዋላል። በታዳጊ ቡድን ውስጥ የበለጠ ለማጥቃት የተጋለጠ አጨዋወት ላይ ይሳተፍ የነበረ ቢሆንም ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ግን በደብል ፒቮት ሚና አንደኛው የተከላካይ አማካይ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የማይኖ ጉልበት እና ግላዊ ኘሬስ አደራረጉ ግሩም ነው። ከ50 በላይ አንድ ለ አንድ የመከላከል ጨዋታዎችን ማሸነፍ ከቻሉ የማንቺስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች መካከል በስኬታማነቱ በሶስተኛ ደረጃ እናገኘዋለን።
ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት ሲጋለጥ ለመከላከል የሚያደርገው ሩጫም ጥሩ የሚባል ነው። ከዚህ በተጨማሪም አደጋን የማሽተት አቅሙ እና እንደአስፈላጊነቱ የቦታ ለውጥ የማድረጉ ነገርም ለቡድኑ ጉልህ አስተዋፅኦን እንዲጫወት አድርጎታል፤ በአጠቃላይ ለመከላከሉ ጥሩ እገዛ የሚያደርግ ተጫዋች ነው።
ማይኖ ከኳስ ጋር
ከኳስ ጋር ማይኖ ቀልጣፋ ሲሆን ከጫናዎች ራሱን ማፅዳት ይችልበታል። በጠባብ ቦታዎች ላይ የኳስ ቁጥጥርን በማስጠበቅ እና ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመጫወት ሂደት ላይ ሲቸገር አይስተዋልም፤ በተለይም ደሞ በፒቮት ቦታ ላይ ካለው አጋሩ ጋር በጥሩ መልኩ ይጫወታል፤ በመጨረሻ ደቂቃ ወልቭስ ላይ ያስቆጠራት የማሸነፊያ ግብ የዚህ ማሳያ ነች።
ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ቅልጥፍናው ወደፊት እንዲጫወት እና የኳስ ቁጥጥርን እንዲያስጠብቅ ያግዘዋል። በኳስ መቀባበል ሂደት ላይ ቅርብ ያለው የቡድን ጓደኛው በደንብ ማርክ ከተደረገ እና ወደ ፊት ለመጫወት የማያስችለው ሁኔታ ላይ ካለ ተመልሶ ኳሱን ተቀብሎ ስፔሶችን ለመጠቀም አይቸገርም።
ቅልጥፍናውና እና ያለው ሚዛኑን የማስጠበቅ አቅም ኳሱን በአዲሱ ቦታው ላይ በቀላሉ ተቀብሎ ወደፊት የሚደረገውን ማጥቃት እንዲያስቀጥል ያግዘዋል።
በመጀመሪያ ጨዋታው ላይ የሚያሻግራቸው ኳሶች ትክክለኛ አልነበሩም፤ ከዚህ በተጨማሪም ተሻጋሪ ኳሱን በሚያግዙ ሩጫዎች የተደገፉ አልነበሩም። ሌላው ረጃጅም ኳሶቹ ላይ የመመጠኑ ነገርም ጥሩ ሳይሆን ተስተውሏል፤ እነዚህ ነገሮች ይበልጥ እድል እያገኘ በሄደ ቁጥር እንደሚስተካከሉ እሙን ነው።
ደብል ፒቮት
ማይኖ የዩናይትድን ዋና ቡድን የተቀላቀሉው በ4-2-3-1 ቅርፅ ውስጥ ከሚገኙት ደብል ፒቮቶች አንዱ በመሆን ነው። በመጀመሪያ 10 የሊግ ጨዋታዎቹ ከካስሜሮ፣ ኤሪክሰን እና ማክቶሚናይ ጋራ መጫወት ችሏል። ማይኖም ከነዚህ ተጫዋቾች ጋራ ጥሩ የሆነ የሜዳ ላይ ተግባቦት እንዳለው ለማስተዋል ተችሏል።
ማይኖ ከካስሜሮ ጋር ሲጣመር በቢውልድ አፑ ላይ ለማጥቃቱ መስመር ቀረብ ብሎ የሚጫወት ሲሆን በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት( ምሰል 1ን ይመልከቱ) በትሪያንግሉ አናት ላይ ሆኖ ቡርኖን ከመከላከል ክፍሉ ጋር ያገናኛል። የኤሪክ ቴንሀጉ ዩናይትድ የክንፍ መስመር አጥቂዎችን ከመስመር ተከላካዮች ጋር በማጣመር ሲጫወት ይስተዋላል፤ ማይኖም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን ሚና ይወጣል፤ አንዳንዴ ካስሜሮን በቢውልድ አፑ ለማገዝ በጥልቀት ሊጫወት ይችላል፤ አሁንም ቢሆን ግን በ10 ቁጥር እና በካስሜሮ መሀል ነው የሚሆነው።
ከኤሪክሰን ጋር ሲጣመር ደግሞ ኤሪክሰን የበለጠ የማጥቃት ባህርይ ያለው አማካይ በመሆኑ ማይኖ በጥልቀት ለመጫወት ይገደዳል። በዚህ ጊዜም ማይኖ ዋና ፒቮት በመሆን ለተከላካይ ክፍሉ ቀረብ ብሎ ይጫወታል። ዩናይትድ ሜዳውን አስፍቶ ሲጫወት ቡርኖ በአንድ በኩል ካስሜሮ በአንድ በኩል( ምስል 2ትን ይመልከቱ) ይሆኑና ማይኖ እነዚህን የቡድን ጓደኞቹኝን የማገናኛ መስመር በመሆን ያገለግላል።
በሌላ በኩል ከማክቶሚናይ ጋር ሲጫወት ተጫዋቹ( ማክቶሚናይ) ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል የዘገዩ ሩጫዎችን በሚያደርግበት ጊዜ ማይኖ ኋላ ላይ ይቆይና የመከላከል ክፍሉን ያስጠብቃል። ማክቶሚናይ ከጥልቅ ቦታዎች ላይ በጫና ውስጥ ሆኖ ኳሶችን በማቀበል ረገድ ጥሩ የሆነ ችሎ አለው። በዚህ አጋጣሚም ከማይኖ ጋር በመተባበር ስለሚሰሩ ያለውን ኳስ የማቀበል ችሎታ አውጥቶ እንዲያሳይና ለቡርኖ ጥሩ እድሎችን እንዲፈጥር ያስችለዋል።
የመከላከል ጥንካሬ
ማይኖ ከማንም ጋር ይጣመር በመከላከሉ ረገድ የሚሰጠው አገልግሎት ተመሳሳይ ነው፤ እንደ ደብል ፒቮትነቱ ' high press'ን በመቋቋም እና እያጠቁ ለሚገኙ የመስመር ተከላካዮች( full-backs) የሚሰጠው ሽፋን አስፈላጊ ነው። የመሀል ክፍሉን በመጠበቅ በኩልም ጥሩ ሚና ሲወጣ ተመልክተናል።
በCV Academy የተዘጋጀ
© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu