የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን አዘጋጆች ሁለት የኬንያ አትሌቶች ላይ ምርመራ ከፈቱ!
የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ላይ ሁለት ኬንያውያን አትሌቶች አንድን ቻይናዊ አትሌት አውቀው እንዲያሸንፍ ሲያደርጉት የሚያሳየው ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
ባሳለፍነው እሁድ የተካሄደው የቤጂንግ ማራቶን ሊገባደድ ሲል አራት አትሌቶች ወደመጨረሻ መስመሩ ላይ መቃረብ ይጀምራሉ ሁለቱ ከኬንያ ( ሮበርት ኬተር እና ዊሊ ምናንጋት) ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያው ደጀኔ ሀይሉ ነው። ከነሱ ጋር ሂ ጂ የተሰኘ ቻይናዊ አትሌት አብሮ ይገኛል፤ ከጀርባቸው ተነስቶም ሲቀድማቸው እና ሲያሸንፍ ታይቷል።
ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ የቤጂንግ ስፖርት ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ግለሰብ ለአሶሼትድ ኘሬስ " ጉዳዩን እያጣራን እንገኛለን፤ አጣርተን የደረስንበትን ለህዝቡ ይፋ እንደርጋለን" ብለዋል።
X step የተሰኘው የቻይናው የስፖርት ብራንድ ዝግጅቱን ስፖንሰር ያደረገ ሲሆን ከሂ ጂ ጋርም ኮንትራት አለው፤ ተቋሙ " The paper" ለተሰኘ የሀገር ውስጥ ሚዲያ እንደገለፀውም በርካታ አካላት ጉዳዩን እያጣሩት ይገኛሉ።
በቪዲዮ ላይ እንደሚታየው ሂ ጂ የመጨረሻዎቹ 100 ሜትሮች ላይ ከጀርባ ሆኖ ይታያል። በመቀጠልም ሌሎቹ አትሌቶች ሲያቀዘቅዉ እና አንደኛው ኬንያዊ አትሌት ለቻይናዊው ሂ ጂ ውድድሩን እንዲመራ እና እንዲያሸንፍ ምልክት ሲሰጠው ይታያል።
ሂ ጂ ከሶስቱ አትሌቶች በ1 ሰከንድ ቀድሞ ነው ማሸነፍ የቻለው። " ከዚህ በፊት በግማሽ ማራቶን ላይ ተሳትፌ አላውቅም እናም ዛሬ የራሴን ምርጥ አቋም ለማሳየት ፈልጌ ነበር" ሲል ተናግሯል፤ ከዚህ በተጨማሪም ውድድሩን ለመጪው የፓሪስ ኦሎምፒክ እንደመዘጋጃ እንደሚያየው ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም እባካችሁ በቻይናውያን አትሌቶች እመኑ በፓሪስ የቻይናውያንን ፍጥነት ለአለም እንደማሳይ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ተናግሯል።
ሂ ጂን አውቆ እንዲያልፍ ያደረገው አንደኛው ኬንያዊ አትሌት በቻይናዊ ወኪል መወከሉም ሌላ ጥርጣሬን ፈጥሯል።
© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu