4-3-2-1 ከጀርባ በሁለት የመሀል ተከላካዮች፣ እና ሁለት የመስመር ተከላካዮች የተገነባ ሲሆን ከነዚህ ተከላካዮች ፊትለፊት 'flat' በሆነ መልኩ የተጣመሩ ሶስት አማካዮች ይገኛሉ።
ይሄ የአማካይ ክፍል በሌሎች ሁለት የ10 ቁጥር ተጫዋቾች የሚጠናከር ሲሆን ከነሱ ፊት ደግሞ ዋናው ጨራሽ አጥቂ ይገኛል።
4-3-2-1 የ'ክሪስማስ ትሪ' ፎርሜሽን ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ ነው?
4-3-2-1 ቅርፁ ከክሪስማስ ትሪ ጋር ስለሚመሳሰል በብዛት ' የክሪስማስ ትሪ' ፎርሜሽን እየተባለ ይጠራል።
4-3-2-1 እንዴት ተፈጠረ?
4-3-2-1 ከእውቁ 4-3-3 አሰላለፍ መነሻነት እንደተፈጠረ ይነገራል፤ እንደሚታወቀው በ4-3-3 ሁለት አስፍተው የሚጫወቱ የማጥቃት መስመር ተጫዋቾች ይኖራሉ፤ እነዚህ ተጫዋቾች የ10 ቁጥር ሚና ተሰቷቸው ሲጫወቱ ቅርፁ 4-3-2-1 ይሆናል።
Inverting the pyramid የተሰኘውን መፅሀፍ እንደፃፈው ጆናታን ዊልሰን ገለፃ ከሆነ ይህ ፎርሜሽን ለእግር ኳስ የተዋወቀው በአሰልጣኝ Adriaanse አማካኝነት ነው።
በ1994 ' ክሪስማስ ትሪ' የተሰኘው ይህ ፎርሜሽን በእንግሊዝ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ።
ቡድኑ ኳስ ሲይዝ በ4-3-2-1 የሚጫወት ቡድን ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ያለባቸው ሀላፊነት ምንድነው?
ፊትለፊት ያለው ብቸኛው አጥቂ በተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች መሀል እና ዙርያ አካባቢ ያለውን ክፍተት እያነፈነፉ መቆጣጠር ይኖርበታል። የዚህ አጥቂ ሚና ኳሱን መያዝ ወይም ደሞ ከአጋዦቹ 10 ቁጥሮች ጋር ማገናኘት አልያም ከተከላካዮች ጀርባ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ለ10 ቁጥሮቹ ክፍተት( space) መፍጠር ነው።
10 ቁጥሮቹ ከጨራሹ አጥቂ ጋር እየተለዋወጡ ጥልቅ ሩጫዎች ያደርጋሉ፤ ከዚህ በተጨማሪም በመስመሮች መሀል ስራቸውን ይከውናሉ። አንደኛው 10 ቁጥር ሜዳውን አስፍቶ ኳስ በመቀበል የተቃራኒ ቡድንን ፉልባክ ላይ ጥቃት ሲሰነዝር መመልከትም የተለመደ ነው።
ሶስቱ የመሀል አማካዮች ወደፊት ሩጫዎችን በማድረግ ማጥቃቱን ያግዛሉ። የትኛውም የመሀል አማካይ አስፍቶ መጫወት የለበትም፤ ይሄ በሚሆንበት ጊዜ ፉልባኮቹ ወደፊት መሄድ እና ለማጥቃቱ ጥልቀት ሊጨምሩ ይችላሉ።
ቡድኑ ከኳስ ውጭ ባለው እንቅስቃሴስ የተጫዋቾች ሚና ምን ይሆናል?
4-3-2-1 ጠባብ የሆነ ፎርሜሽን ስለሆነ የመሀል ክፍሉ በሚገባ የተጠበቀ ይሆናል። ጨራሹ አጥቂ እና ሁለቱ 10 ቁጥሮች የተቃራኒ ቡድን የኋላ መስመርን ' ኘሬስ' ማድረግ ወይም ደግሞ ለተቃራኒ ቡድን የመሀል ክፍል የተላኩ ኳሶች እንዳይደርሱ መጋረድም ይችላሉ።
ተቃራኒ ቡድን ሜዳውን አስፍቶ በሚጫወትበት ጊዜ ቅርብ ያለው 10 ቁጥር ወይም የመሀል አማካዩ ' ኘሬስ' ያደርጋል፤ ብዙ ጊዜም ከጎኑ ባለው አማካይ እገዛ ያገኛል። በተቃራኒ አቅጣጫ የሚገኙት ተጫዋቾችም ሜዳውን እያጠበቡ ይመጣሉ ይህም ተጨማሪ የመከላከል እገዛን ይሰጣል። የመሀል አማካይ ላይ የሚገኘው የሶስትዮሽ ጥምረትም ወደተቃራኒ ቡድን የፊት መስመር ኳስ እንዳይደርስ ይጋርዳል።
4-3-2-1 የተጠቀሙ ቡድኖች እነማነቸው?
1/ የአንቼሎቲ ኤሲሚላን
አንቼሎቲ 4-3-2-1ን ተጠቅመው በ2003 እና በ2007 ሻምፒዮንስ ሊግን ማሳካት ችለዋል። ፎርሜሽኑ የተገነባውም እንደ መሀል ' ፒቮት' በሚጠቀሙት አንድሪያ ፒርሎ ነበር።
2/ የናግልስማን ሌብዢግ
ናግልስማን በጀርመኑ ክለብ ቆይታው ተለዋዋጭ አቀራረቦች ይዞ በመምጣት ቢታወቅም በብዛት 4-3-2-1ን ይጠቀም ነበር።
3/ ሳሬ በጁቬንቱስ
ሳሬ በጁቬንቱስ ቆይታው በ4-3-2-1 ነበር የሚያጠቃው፤ ክሪስትያኖ ሮናልዶም የጨራሽ አጥቂ ሚና ይኖረዋል። ዲባላ፣ ቤርናርዴስኪ እና ራምሴ በ10 ቁጥር ቦታ ላይ ሲጫወቱ፤ ፒያኒች ብቸኛው ' ፒቮት' በመሆን የኋላ ክፍሉን እና 10 ቁጥር ተጫዋቾችን ያገናኝ ነበር።
በ4-3-2-1 መጫወት ምን ጥቅም አለው?
በ4-3-2-1 ፎርሜሽን መጫወት መሀል ላይ በርካታ ተጫዋቾች እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህም ቡድኑን መሀል ላይ ኳሱን በደንብ እንዲቆጠጣር እና በዚያ በኩል ለሚደረጉ የመልሶ ማጥቃቶች ሽፋን እንዲያገኝ ያስችለዋል።
ሁለቱ 10 ቁጥሮች ለመከላከል ከባድ ናቸው፤ በተለይም የጨራሹ አጥቂ አቋቋም ክፍተት ፈጥሮላቸው በቁልፍ ቦታዎች ላይ ኳስ እንዲቀበሉ ካደረጋቸው ለመከላከል እጅግ አስቸጋሪ ይሆናሉ።
ቡድኑ የሚያጠቁ ፉልባኮችን ከያዘ ደግሞ ብዙ ክፍተቶች ስላሉ ወደፊት ገፍቶ ለመጫወት አይቸገሩም።
በ4-3-2-1 መጫወት ጉዳቱስ?
4-3-2-1 ጠባብ ፎርሜሽን ከመሆኑ የተነሳ በተቃራኒ ቡድን የመከላከል ሽግግር ወቅት ሜዳውን አስፍተው ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፉልባኮቹ የሚሄዱበት መስመር ባዶ ስለሆነ በዚያ በኩል ተቃራኒ ቡድን ወደፊት እንዲያጠቃ በር ይከፍታል።
ሜዳውን አጥብበው በመጫወታቸው የሚመጡ ክፍተቶችን ለመሸፈን ተጫዋቾች ከመጀመሪያ ሚናቸው ለቀው እንዲሄዱ ያስገድዳል፤ ይሄም በታክቲክ እና በቴክኒክ እጅግ የላቁ ተጫዋቾችን የሚጠይቅ ነው።
4-3-2-1
Credit: The coaches voice
© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu