Nav And Top Bar

ሁለት ሊጎች በቀጣይ የውድድር ዘመን ተጨማሪ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ያገኛሉ

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከቀጣይ የውድድር ዘመን ጀምሮ የ36 ቡድኖች ውድድር መሆኑን ተከትሎ ሁለት ሊጎች ተጨማሪ አምስተኛ ቡድን በሻምፒዮንስ ሊግ እንዲያሳትፉ እድል አግኝተዋል።

እነዚህ ሁለት ሊጎች እንዴት ይለያሉ?

ተጨማሪ አምስተኛ ቦታ ለእያንዳንዱ ሀገር በአውሮፓ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦች በሚያስመዘግቡት አማካይ ነጥብ ላይ የተመረኮዘ ነው፤ የእያንዳንዱ ክለብ የአውሮፓ ውጤት ተሰልቶ ይጨመቅና ለሊጉ ነጥብ ይሰጣል በዚያ ነጥብ አማካኝነትም 1ኛ እና 2ኛ የሆኑት ሊጎች በቀጣይ የውድድር ዘመን አምስተኛ ቡድን በሻምፒዮንስ ሊጉ የሚያሳትፉ ይሆናል።

በአውሮፓ ውድድሮች እያንዳንዱ ክለብ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ 2 ነጥብ ያገኛል፤ አቻ ከወጣ ደግሞ አንድ ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን ጨዋታው በ90 ደቂቃ ካላለቀና እስከ 120 ደቂቃ ድረስ ከሄደ ከ120 ደቂቃ በኋላ ያለው ውጤት ከግምት ይገባል። የመለያ ምት ከግምት ውስጥ አይገባም፤ የ120 ደቂቃው ውጤት ታይቶ እንደአቻ ተቆጥሮ ለየክለቦቹ 1 1 ነጥብ ነው ሚሰጠው።

ክለቦች የሆነ ደረጃ ሲደርሱ የሚሰጥ ጉርሻ ነጥብም አለ፤ የጉርሻ ነጥቡን አሰጣጥ ስንመለከት:

ሻምፒዮንስ ሊግ ጉርሻ ነጥብ

4- ምድብ ጨዋታዎች መካፈል ለቻለ
5- 16 ውስጥ መግባት ለቻለ
1- ሩብ ፍፃሜ፣ ግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ መድረስ ለቻለ

ኢሮፓ ሊግ ጉርሻ ነጥብ

2- የየምድቡ አንደኛ ጨራሽ ለሆነ
1- የየምድቡ ሁለተኛ ጨራሽ ለሆነ
1- ግማሽ ፍፃሜ፣ ፍፃሜ መድረስ ለቻለ

ኮንፍረንስ ሊግ ነጥብ

2- የየምድቡ አንደኛ ጨራሽ ለሆነ
1- የየምድቡ ሁለተኛ ጨራሽ ለሆነ
1- ግማሽ ፍፃሜ፣ ፍፃሜ መድረስ ለቻለ

በመጨረሻም በየክለቦቹ የተገኙ ነጥቦች ይደመሩና አጠቃላይ ውጤቱ ሀገሪቷን ወክለው በአውሮፓ እየተካፈሉ ላሉ ቡድኖች ብዛት ይካፈላል። ይህም የየሊጎቹን አማካይ ' coefficient ' ይሰጠናል።

ለምሳሌ አንድ ሀገር በክለቦቹ 35 ነጥብ ቢያስመዘግብና 7 ክለቦች በአውሮፓ ውድድሮች እያሳተፈ ቢገኝ አማካይ ' coefficient ' 5 ይሆናል ማለት ነው( 35/7=5)

ታዲያ የዘንድሮው የየሊጎቹ ' coefficient average' ምን ይመስላል?

1/ ጣሊያን - 19.428
2/ ጀርመን- 18.357
3/ እንግሊዝ- 17.375
4/ ፈረንሳይ- 16.083
5/ ስፔን- 15.437
6/ ቤልጅየም- 14.200
7/ ቼክ- 13.500
8/ ቱርክ- 12.000
9/ ፖርቹጋል- 11.000
10/ ኔዘርላንድስ- 10.000

የዶርትመንድ የትላንትናው አሸናፊነትም ተጨማሪ ነጥብ ማስገኘት ስለቻለ ቦንደስሊጋ ሁለተኛ ደረጃውን ማንም እንደማይቀማው ለማረጋገጥ ተችሏል፤ ጣሊያን 5 ክለቦችን እንደምታሳትፍ ቀደም ብላ ማረጋገጥ የቻለች ሀገር ነች።

አንድ ሀገር በቀጣይ የውድድር ዘመን 5 ክለቦች እንደሚያሳትፍ መቼ ማወቅ ይቻላል?

በበርካታ የውድድር ዘመኖች መጋቢት ላይ ይህን በግልፅ ማወቅ ሚቻል ይሆናል፤ ምክንያቱም በሶስቱም የአውሮፓ ውድድሮች የትኞቹ ቡድኖች ወደሩብ ፍፃሜ መግባታቸውን ስለምናውቅ አንደኛ እና ሁለተኛ ሚጨርሱትን ሊጎች ለማወቅ አያዳግትም፤ ዘንድሮ በአውሮፓ ውድድሮች ሩብ ፍፃሜ ከደረሱ 5 የእንግሊዝ ክለቦች 4ቱ መሰናበታቸው ቦታውን በጀርመን እንዲነጠቁ አድርጓል።

በአዲሱ አሰራር መሰረት አንድ ሀገር እስከ 11 የሚደረሱ ክለቦችን በአውሮፓ ውድድሮች( UCL,UEL እና Conference League) ሊያሳተፍ የሚችልበት አጋጣሚ አለ፤ ሰባቱ የተለመደው አሰራር( 4 በሻምፒዮንስ ሊግ፣ 2 በኢሮፓ ሊግ እና 1 በኮንፍረንስ ሊግ) ከዚያ ደሞ በአማካይ ' coefficient ' ስሌት 1ኛ ወይም 2ኛ የወጣ ሀገር ከሆነ አንድ ተጨማሪ ቡድን በሻምፒዮንስ ሊግ፣ ሌላው ደግሞ በሶስቱም ውድድሮች አሸናፊ ሆነው የጨረሱት የሀገሪቷ ክለቦች ከሆኑ( የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ- በቀጣይ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ያገኛል፤ የኢሮፓ ሊግ ደግሞ በሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ያገኛል እና የኮንፍረንስ ሊግ አሸናፊ ደግሞ በኢሮፓ ሊግ ቦታ ያገኛል)

በአሁኑ ሰአት ባለው ደረጃ አምስተኛ የወጣ ሻምፒዮንስ ሊግ ይገባል በሚለው የሚጠቀሙት በሀገራቸው የአምስተኛ ደረጃን ይዘው የሚገኙት ቦሩሲያ ዶርትመንድ እና ኤኤስ ሮማ ናቸው።

ምንጭ: ኢኤስፒኤን እና የቦንደስሊጋ ይፋዊ ድረ-ገፅ

Yonatan Ayele
Footer
Get In Touch

Yonatan Ayele

yonatan@eskaysportet.com

Follow Us

© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu