Nav And Top Bar

የሊጉ የመጨረሻ ቀን እንዴት ያለ ነው? ዋንጫው በምን መልኩ ይዘጋጃል?

የሶስት ፈረሶች እሽቅድምድም መስሎ የነበረው የ2023/24 የእንግሊዝ ኘሪምየር ሊግ ሊቨርፑልን ከጨዋታ ውጭ አድርጎ ማንቺስተር ሲቲ እና አርሰናልን ለሊጉ የዋንጫ ክብር አፋጧል። በእለተ እሁድ 12:00 ሲልም ሁሉም ጨዋታዎች በእኩል ሰአት የሚጀምሩ ይሆናል።

የሊጉ ዋንጫ አሸናፊ በመጨረሻው ሳምንት ሲረጋገጥ ይሄ ለ10ኛ ጊዜ ነው። እንደ ኦኘታ መረጃ መሰረት ማንቺስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ቶተንሀም ሆትስፐርስን ካሸነፈ በኋላ ሊጉን የማሸነፍ እድሉ ከ25 መቶኛ ወደ 84 መቶኛ ከፍ ብሏል፤ የአርሰናሎች ደግሞ ወደ 16 መቶኛ ወርዷል።

በእለቱ በሄሊኮፕተር አንድ ዋንጫ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ ይልቅ ሁለት ዋንጫዎች ተዘጋጅተው በሁለቱም ስታድየሞች የሚቀመጡ ይሆናል። ሁለቱም ዋንጫዎች ከዚህ ቀደም በሻምፒዮን ቡድኖች የተነሱ ናቸው።

በውድድር ዘመኑ አንደኛው ዋንጫ ከዚህ ቀደም በነበረው አመት ዋንጫውን ካሳካው ቡድን ጋር የሚቆይ ሲሆን ሌላኛው ተመሳሳይ ዋንጫ ደግሞ በሊጉ አገልግሎት ላይ ይውላል። የአምና ዋንጫ አሸናፊዎቹ ማንቺስተር ሲቲ ከመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ 3 ሳምንታት ቀድመው የወሰዱትን ዋንጫ ለሊጉ መመለስ ስላለባቸው፤ ያንን አድርገዋል።

በኢሜሪትስም ሆነ በኢትሀድ 40 40 ሜዳሊያዎች የሚዘጋጁ ይሆናል። እኚህ ሜዳሊያዎች ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ ለስታፍ እና በሊጉ ቢያንስ 5 ጨዋታዎችን ለተጫወቱ ተጫዋቾች የሚበረከት ይሆናል፤ ስለዚህ አንድ ተጫዋች በቡድኑ ቢያንስ 5 ጨዋታዎችን ማድረግ ከቻለ የኘሪምየር ሊግ ዋንጫን እንዳነሳ ይቆጠርለታል ማለት ነው።

የኘሪምየር ሊግ ዋንጫ ዲዛይን 'ሶስቱ አናብስት' ከተሰኘው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን መጠሪያ ጋር ተያያዥነት አለው። ሁለት አናብስት ከእጀታው በላይ በግራ እና በቀኝ የሚገኙ ሲሆን የዋንጫ አሸናፊው ክለብ አምበል ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ሲያነሳ እርሱ ደግሞ 'ሶስተኛው አንበሳ' ይሆናል ማለት ነው። ዋንጫው 104 ሴንቲሜትር የሚረዝም ሲሆን 61 ሴንቲሜትር ስፋት አለው፤ ከዚህ በተጨማሪም 25 ኪሎ ግራም ይመዝናል።

ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ያሳካው የ2003/04 የአርሰናል ' invincibles' ቡድን አባላት ዛሬ 20ኛ አመት መታሰቢያ በአላቸውን የሚያከብሩ ሲሆን ነገ በሚደረገው የሊጉ መዝጊያ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዘዋል። የአሁኑ የአርሰናል ስፖርቲንግ ዳይሬክተር የሆነው ኤዱም የቡድኑ አባል እንደነበር ይታወሳል።

አርሰናል የሊጉን ዋንጫ የሚያሸንፍ ከሆነ የፊታችን ሰኞ በግንቦት 20,2024 የሶስት ሰአት የክፍት ባስ ጉዞ በ' islington' ጎዳናዎች የሚያደርግ ይሆናል። ማንቺስተር ሲቲ  ለቀጣዩ ወሳኝ የዋንጫ ጨዋታ ላለመዘነጋት ሲባል ዋንጫ የሚያነሱ ከሆነ በክፍት ባስ ከተማቸውን ለመዞር በመጪው ግንቦት 25,2024 የሚደረገውን የኤፍኤ ካኘ ፍፃሜ ጨዋታ ይጠብቃሉ።

አሊሰን ብሪታን የተሰኙት የሊጉ የቦርድ ሊቀመንበር በኢትሀድ የሚገኙ ሲሆን ሪቻርድ ማስተርስ የተሰኙት የሊጉ ስራ-አስፈፃሚ  ደግሞ በኢሜሬትስ ስታድየም የሚገኙ ይሆናል።

የሊጉ ስራ-አስፈፃሚ ማስተርስ ማንቺስተር ሲቲ ስለቀረበበት 115 ክሶች በተመለከተ ባሳለፍነው ወር " በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳብ መስጠት አንችልም፤ ጉዳዩ የሚፈታበት ቀን ተቀምጧል፤ በቅርቡም ይፈታል" ብለዋል።

ማንቺስተር ሲቲ የቀረበበትን 115 ክሶች ለመስማት በጥቅምት አልያም በህዳር ቀነ-ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን ውሳኔው በክረምት 2025 እንደሚተላለፍ ይጠበቃል። ማንቺስተር ሲቲዎች በተደጋጋሚ ከክሶቹ ንፁህ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዘገባውን ስናጠናቅር ኒውዮርክ ታይምስን ተጠቅመናል።

ግንቦት 10, 2016 አ.ም

SKY ስፖርት ET™

Yonatan Ayele
Footer
Get In Touch

Yonatan Ayele

yonatan@eskaysportet.com

Follow Us

© SKY ስፖርት ET™. All Rights Reserved.
Developed by Gashu